group-telegram.com/HakimEthio/33412
Last Update:
ነብሰ ጡር እናት ወይም አጥቢ እናት መጾም ትችላለች?
እንደሚታወቀው አንዲት እናት በእርግዝናዋ ጊዜ ወይም ጡት በምታጠባበት ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ የተሻሉ እና በዛ ያሉ ምግቦችን መመገብ እና ፈሳሾችን ማብዛት ይጠበቅባታል። ከሌላው የእድሜ ክፍል በተለየ ሁኔታ የተመጣጠነ ምግብ የሰፈልጋታል።
ነፍሰ ጡር እናት ከሆነች ደሞ በተለየ ሁኔታ የመጀመሪያዎቹ 3 ወራት ላይ በተደጋጋሚ ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ ስለሚያጋጥሟት በአንጻሩ ደግሞ በመጨረሻዎቹ ወራት ቶሎ የመጥገብ እና የምግብ ፍላጎት መቀነስ ስለሚከሰትባት በ24 ሰአት ዉስጥ ከ 5 ጊዜያት በላይ መመገብ ሊያስፈልጋት ይችላል።
ይህም በመሆኑ አንዲት ነብሰ ጡር ወይም አጥቢ እናት ለመጾም ከመነሳቷ በፊት ቀጥሎ ያሉትን ህክምናዊ ጉዳዮችን ማወቅና አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ መውሰድ እንደሚገባት ለማስታወስ እንወዳለን ፦
በመጀመሪያዎቹ 3 ወራት የእርግዝና ጊዜ የሚገጥሙ ማስመለስ እና ማቅለሽለሽ ካለ በጾም እንደሚባባስ ማወቅ ያስፈልጋል
አንዲት ነብሰ ጡር ወይም አጥቢ እናት የስኳር በሽታ ካለባት ለእርሱም መድሃኒት የምትወስድ ከሆነ ጾም ላይ መጠንቀቅ ይገባታል
የደም ማነስ ፣ ተቅማጥ ፣ ደም ግፊት አንዲሁም ሌሎች ከእርግዝና ጋር ወይም ከ ማጥባት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ተጨማሪ ህመሞች አለመኖራቸውን ማወቅ ይኖርባታል
በጾም ምታሳልፈው የቀኑ እርዝመት ከ 12 ሰአት እንዳይበልጥ ይመከራል
የአካባቢው የአየር ሁኔታ በጣም ሞቃታማ ከሆነ አለመጾሙ ይመከራል
ሱሁር መመገብ ፣ ጨው የበዛበትን መግብ መቀነስ ፣ በአንጻሩ ደሞ በተለይ ስሁር ላይ ፕሮቲን ፣ ፋይበር ነክ የሆኑ ጥሩ ምግቦችን መመገብና ፈሳሽ ነገሮችን በብዛት መውሰድ ይመከራል
ለመጾም ሲወስኑ ሃኪሞን ሳያማክሩ በአርግዝና ወቅት የሚሰጡ መድሀኒቶችን ማቁአረጥ እንደማይገባ ማወቅ ግድ ይላል
መንታ ወይም ከዚያም በላይ ጽንስ ካለ ከአምስት ወር በኀላ አለመጾሙ ይመከራል
አሁን ላይ የምጥ ሰሜቱ ካለም መጾም አይመከርም
ከላይ የተዘረዘሩትን ቅድም ጥንቃቄዎችን ያረገች እናት ረመዳኑአን በየትኛውም የእርግዝና እድሜ ላይ ብትጾም ፅንሱ ላይ ችግር እንደሌለው በርካታ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ከዘጠኝ ወር ጊዜ ውስጥ አንድ ወር መፆም ጉዳት እንደሚያስከትል የሚአትት የጥናት ውጤት እንደሌለም ይታወቃል ። ሆኖም ግን እርግዝና ላይ ያለች እናት ከሚያስፈልጋት ጉልበት አኳያ ፆሙን ጀምራ ካልቻለች ወይም የድካም ስሜት ከተሰማት ቀጥሎም ራስ ምታት ከተሰማት በጾሙ መቀጠል አይገባትም። የመፆም ፍላጎቷ ካየለ ግን አንድ ቀን እየፆመችና አንድ ቀን እያፈጠረች አቅሟን እንድታይ ትመከራለች።
ፆመኛ የሆነች ነብሰ ጡር ወይም አጥቢ እናት እንዳትወስዳቸው የምትመከራቸው የምግብ አይነቶች
ጨው የበዛበት ምግብ ፣ ቅባትና ጮማ፣ ስኳር የበዛበት ምግብ
እንደማንኛውም ጊዜ ከሱስ ሁሉ መጠንቀቅ
ፆመኛ የሆነች ነብሰ ጡር ወይም አጥቢ እናት (በተለይ ስሑር ላይ) እንድተወስድ ምትመከራቸው የምግብ አይነቶች
በፕሮቲን የበለጸጉ የምግብ አይነቶችን (ለምሳሌ ለውዝ ፣ ምስር፣ አተር ወይም የባቄላ ፉል
በፋይበር የበለጸጉ የምግብ አይነቶችን (ለምሳሌ ተምር)
ፍራፍሬዎችን (ለምሳሌ የማንጎ ፣ የአቮካዶ ፣ የፓፓዬ ፣ ወዘተ ጭማቂዎችን
ሆልግረይን ምግቦችን (ለምሳሌ የቂንጬ ሾርባ ፣ ውሃ በወተት)
በፆመ ላይ የሆነች ነብሰ ጡር ወይም አጥቢ እናት የሚከተሉትን ምልክቶች ካየች ሀኪሟን እንድታማክር ትጠየቃለች
- የምጥ ምልክት
- ረዘም ላለ ሰአት የልጅ እንቅስቃሴ መቀነስ
- ከፍተኛ የሆነ ራስ ምታት ማጋጠም
-ከፍተኛ የሆነ ድካም ፣ የውሃ ጥም ፣ ረሃብና ማዞር መከሰት
በጥቅሉ በጾሙ ምክንያት የሚመጣ ምልክቶችን መገምገም
በዶ/ር ሰይድ አራጌ: የማህጸንና ፅንስ ስፔሻሊስት ሀኪም ፣ ረዳት ፕሮፌሰር ፣ ማተርናል ፌታል ሜድስን ሰብ ስፔሻሊስት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል MFM unit እና በረካ የእናቶችና ህጻናት ህክምና ማዕከል
አዲስ አበባ
@HakimEthio
BY Hakim

Share with your friend now:
group-telegram.com/HakimEthio/33412