group-telegram.com/beteafework/5727
Last Update:
በእንተ ንስሐ በቅዱስ ኤፍሬም
"...ሁል ጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ እንጂ ሁል ጊዜ በጥፋት መንገድ አትመላለሱ፤ ሞት ሳታስቡት በድንገት ይመጣባችኋልና፡፡ የሥጋ ምቾትም ንስሓን አይፈልግምና ለጥፋት ይዳርጋል፡፡
የመጨረሻው ቀን መጥቶ ሳያገኘን በንስሓ መንገድ እንመላለስ፡፡ የማይቀረው ሞት ሲመጣ ሁለተኛው ሞት እንዳያገኘን በቅድስና ሆነን እንጠብቅ፡፡ በሃይማኖት መጽናትም የድካማችንን ፍሬ እናግኝ። በዚህች ዓለም መልካሙን ሥራ ሠርተው ካለፉ ቅዱሳን ጋር የክብር አክሊል እንቀዳጅ ዘንድ፡፡ ሰው ታይቶ የሚጠፋውን የዚህን ዓለም አክሊል ለመቀዳጀት በወታደር እና በሠረገላ ጦርነት ይከፍታሉ፤ ጊዜአዊ የሆነ የዚህን ዓለም ደስታና ሐዘን ለመቅመስ ነው፡፡
እንግዲህ የዚህን ዓለም ዘውድ ለመቀዳጀት ሩጫው ይህን ያህል ከሆነ ዘላለማዊውን ክብር፣ ሰማያዊውን አክሊል ለመቀዳጀት ውድድሩ ምንኛ ታላቅ ይሆን? ስለዚህ ሐዋርያው ‹‹የሚታገል ሁሉ በሁሉ ነገር ይታገሣል፤ እነርሱስ የሚጠፋውንና የሚያልፈውን አክሊል ያገኙ ዘንድ ይበረታሉ፤ እኛ ግን የማያልፈውን አክሊል ለማግኘት እንታገሣለን›› (1ቆሮ. 9፥25-26) አለን፡፡
እንግዲህ እርጉም በሆነው ጠላታችን ላይ ድል እስክናገኝ ድረስ ከተንኮል ሥራውም እስክናመልጥ ድረስ የተጋድሎአችንን መሣርያ ንጽሕና ማድረግ ይገባናል፡፡ ክፉ የሆነው ጠላታችን እኛ ትኁታን ስንሆን ይቀናብናልና ይዋጋናል፡፡ እግዚአብሔር ግን ከጠላት ቀስት የምንድንበት የበለሳን መድኃኒት ሰጠን፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር ያስተማረን የንስሓ መድኃኒት ነው፡፡
በእውነት ለቀረበ፣ ከልቡም ተጸጽቶ ለተመለሰ ይህ መድኃኒት ፍጹም የሚያድን ነው፡፡ ነገር ግን መድኃኒቱ የተሰረቀ በደል ያለበትን ገንዘብ በእጃቸው ይዘው፣ የረከሰ ሰውነታቸውን እየወደዱ በአፋቸው ብቻ ‹‹አድነን›› ለሚሉት አይደለም፡፡
ዳግመኛ በቀደመ ርኵሰታቸው የሚወቀሱትን የወቀሳ ድምፅ ስሙ፡፡ እንደዚሁም በመተላለፋቸው እራሳቸውን እየወቀሱ ዳግመኛ ወደ ጥፋት እንዳይመለሱ የሚጠነቀቁትን ስሙ፤ በግብርም እነርሱን ምሰሉ፡፡ ሕሊናን ሁሉ ወደሚመረምረው ወደ እርሱ ሁለት ልብ ሆናችሁ አትቅረቡ፡፡ የተሰወረውን ሁሉ ያውቃልና በሁለት መንገድ አትመላለሱ፡፡
እንግዲህ ንስሓ ለመግባት ፍጠኑ እንጂ ወደ አረንቋ አትመለሱ፡፡ በቸርነቱ ፍቅር ታጥባችሁ ንጹሐን ሁኑ እንጂ ዕዳችሁ ከተሰረዘላችሁ በኋላ ገንዘቡ እንደ ወደመበት ሰው ዳግመኛ ወደ ዕዳ አትግቡ፡፡
ከምርኮ የተለቀቀ ሰው በምንም መልኩ ዳግመኛ መማረክ፣ ወደ ምርኮው ቦታ ተመልሶ መሔድ አይፈልግም፡፡ ወይም ከግዞት ሥቃይ ከወጣ በኋላ ዳግመኛ መገዛት አይፈልግም፡፡ ነገር ግን ዳግመኛ ወደ ግዞት እንዳይገባ ይጸልያል፡፡ እንግዲህ እናንተም ከገዳይ ቀንበር ከወጣችሁ በኋላ ዳግመኛ እንዳትገዙ ጸልዩ፤ በጥልፍልፉ ወጥመድም እንዳትያዙ ትጉ፡፡"
(ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ - በእንተ ንስሐ በዲያቆን መዝገቡ የተተረጎመ - ገጽ 31-34)
BY ቤተ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
Warning: Undefined variable $i in /var/www/group-telegram/post.php on line 260
Share with your friend now:
group-telegram.com/beteafework/5727